በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ፡
መተርጉማኑ መዝሙር ሁለትን በተረጎሙበት አምድ ላይ
“ላዕለ እግዚአብሔር ወላዕለ መሢሁ” የሚለውን ገጸ ንባብ
አንድ ጊዜ “በእግዚአብሔርና በመሢሁ ላይ” ብለው ሲያልፉት ሌላ ጊዜ ደግሞ “በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ ላይ” እያሉ ዋናዋን ቃል ላለመንካት ዳር ዳር በማለት ሲተረጉሙት በብራ የተጻፈው ትርጓሜ ላይ ግን “በእግዚአብሔር አብም መንፈስ ቅዱስን በቀባው ልጁም” በማለት ተተርጉሞ ይገኛል። ይህ ትርጓሜም የእነ ቅዱስ ቄርሎስን፣ የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ትርጓሜ የተከተለ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ማለት እንግዲህ ከስሙ ትርጓሜ ስንነሳ
ክርስቶስ - በጽርዕ፤
መሲሕ - በአረብ፤
ቅቡዕ - በግእዝ፤
የተቀባ - በአማረኛ ተብሎ ተተርጉሞ በመጽሐፍት እናገኘዋለንና። ዮሐ ፩፥፵፩ ትርጓሜ፤ መጽ ምስጢር 20፥40።
ሌላው ደግሞ መዝሙር 44 ላይ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ስለ ክርስቶስ የተናገረበት ትንቢት ነው።
“መዝሙረ ዳዊት ንባቡና ትርጓሜው” በማለት በ1950 ዓ/ም የታተመውና ከዚያ ጀምሮ ወልድ ቅብዕ ባዮች(ካሮች) “ከጥንት ከኢትዮጵያ ሊቃውንት ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ” በማለት በማር የተለወሠ መርዛቸውን ለትውልድ ሲግቱ እንደሚከተለው እናየዋለን።
"ተከዕወ ሞገስ እምከናፍሪከ ፤ በእንተዝ ባረከከ እግዚአብሔር ለዓለም -- ካንደበትህ ባለሟልነት ሞልቶ ፈሰሰ፤ ስለዚህ ነገር እግዚአብሔርነትህ ለዘላለሙ በተዋሕዶ አከበረህ” ብለው የሌለ ትርጉም፤ እንግዳ ትምህርት በማስገባት ተርጉመውታል።
ከብራናው ላይ ግን ““ተከዕወ ሞገስ እምከናፍሪከ --
ስርየተ ኃጢያት፤ ትምህርት ከአፍህ እንደ ውኃ ፈሰሰ።
በእንተዝ ባረከከ እግዚአብሔር ለዓለም --- ኃጢያት ታስተሰርይ፣ ታምራትም ታደርግ ዘንድ፤ ትምህርትም እንድታስተምር በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ አከበረህ” ይላል።
