የግንደ ወይን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ታሪክ
የደብረፅዮን ቅድስት ማርያም ገዳም የምትገኘው በግንደወይን ከተማ ሲሆን፤ ጊዜው 1500 ዓ.ም ነው በዚህን ወቅት በዚች ላይ የአባ እንጦንዮስ እና የአባ መቃርዮስን ስርዓተ ምንኩስናና ብህቱና ተቀብለው አለምን ንቀው በህብረት የሚያገለግሉ መናኒያን ድምፀአራዊቱን ግርማ ሞገሱን ታግሰው ታቦተ ኪዳንምህረትን ይዘው ይኖሩ ነበር ፡፡
ቦታው በዋሻና በዱር የተከበበ በአራዊት የታጠረ በመሆኑ እነዚህ መናንያን የመረጡት እንደሆነ የገዳሟ ታሪክ ያስረዳል፤ ከቦታው ቅድስናና ታላቅነት እንዲሁም አስፈሪነት የተነሳ በወቅቱ የነበሩ ነገስታትና መኳንንቶች ይህን ቦታ ለማየት ደፍረው አይገቡም ነበር ፡፡
በዚህ ቦታ ይኖሩ ከነበሩ መናንያን መነኮሳት መካከል አባ አቤሴሎም የብሉያት መምህር ፣ አባ አሳሄል የሀዲሳት መምህር እንደነበሩና መንኩስናን ከመምህርነት ጋር አስተባብረው የያዙ መሆናቸውን ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ ፡፡ እነዚህ መናንያን መነኩሳት ይችን ቦታ ሲቆረቁሩ ዝም ብለው አይደለም በእግዚአብሔር ፍቃድና ብዙ መናኒያን ከየቦታው እየተሰባሰቡ ታቦተ ኪዳንምህረትን ይዘው በፆሎት በፆም እየተጉ በአራዊት ተከበው የተጋድሎ ህይወታቸውን ይኖሩ እንደነበር በመልክአ የማነ ክርስቶስ ገድል ላይ በተፃፈ ብራና ላይ እናገኘዋለን ፡፡
እነዚህ መናንያን መነኩሳት በቅድስና ማዕረጋቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በታምራቸው የሚያስደንቅ ገቢረ ታአምራት የፈፅሙ እንደነበር ይኸው የብራና መፅሀፍት ያስረዳል ፡፡ በደጉ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት አባ ድል በጃን እና አስከናፍር የሚባሉ ገዳም አቅኝዎች ታቦተ ፅዮንንና ታቦተ ሚካኤልን ይዘው ብዙ ሀገራትን ቤተ - ክርስቲያን ለመትከል ሲዞሩ ኖረው ዛሬ አባር / በአሁኑ አጠራር አባር ውሃ ቀበሌ ከሚባለው ቦታ ላይ ያርፋሉ ፤ይህ ቦታ አሁን ከገዳሟ 15 ኪ.ሜ በምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል ፡፡ ታቦቱንም ይዘው ድንኳን ሰርተው 40 ዘመን ከቦታው ላይ መነኩሳትን ጨምረው አምልኮተ እግዚአብሔር እየፈፀሙ ከኖሩ በኃላ አንድ ቀን ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ቅዱስ ሰው ተገልፆ ድል በጃንን ‹‹ ታቦተ ፅዮንን ይዘህ ወደ ምዕራብ ሂድ የምትተክልበት ቦታ ታገኛለህ ›› ካላቸው በኋላ አስከናፍርን ደግሞ
ታቦተ ሚካኤልን ይዘህ ወደ ምስራቅ ሂድ ›› አላቸው፡፡አስከናፍርም በተነገራቸው መሰረት ወደ ምስራቅ ሂደው ዛሬ የቡችር ሚካኤል ብለን የምንጠራውን ተከሉ ፡፡
ድል በጃንም እንደተባሉት ታቦተ ዕዮንንና የተወሰኑ መነኩሳትን ይዘው ወደ ምዕራብ ይጓዛሉ ከዚያም በመናንያ የተከበበ ለገዳማዊ ህይወት የሚመች ፀጥታ የሰፈነበት ቀደም ሲል እነ አባ አቤሴሎም ፣ አባ ኣሳሄል እንዲሁም አባ የማነ ክርስቶስ ፣ አባ ወልደ ጊዮርጊስ ፣ አባ ሳዊሮስ ሌሎችም መናንያን ጨምረው ያቀኑት የመናንያን ቦታ ያገኛሉ ። ድል በጃንም ከመናንያኑ ጋር ተቀራርበውና ተመካክረው ታቦተ ፅዮንንና ታቦተ ኪዳንምህረትን በአንድ ላይ አስቀምጠው የህይወቱ መጨረሻ ቦታ ይች ነች ብለው የብህትውና ህይወት አብረው መኖር ጀመሩ ፡፡ ድል በጃንና አባ የማነ ክርስቶስ ፣ አባ ሳዊሮስ የአባ ተጠምቀ መድህን ደቀ መዛሙርት በምናኔ አብረው የኖሩ ስለነበር በጋራ በመሆን ቤተ- ክርስቲያን ለመትከል መምከርና መወያየት ጀመሩ እግዚአብሔርንም በፆሎት ጠየቁ ፤የእግዚአብሔር ፍቃድ እንደሆነ ካወቁ በኃላ የቤተ - ክርስቲያንን የመትከያ ቦታ የት ይሁን ሲሉ ካሳረፉበት ቦታ ላይ ሲመለከቱ ከዚህ የተሻለ እንደማያገኙ አውቀው ለስራው መዘጋጀት ጀመሩ ፡፡ ስራ ሲጀምሩም ከቦታው ላይ የወይን ግንድ አገኙ ፤እነሱም እዚህ ትተከል ስሟም ግንደወይን ትባል አሉ፤ ትርጉሙም የወይን ግንድ ማለትነው ፡፡
ከዚህ በኋላ ድል በጃንም ቤተ ክርስቲያኗን ከምእምናኑ ጋር ከተከሉ በኋላ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው ብዙዎቹ እያረፉ ሌሎች እየደከሙ ሲሄዱ የእነሱን እቃና ሀላፊነት ተረክበው ከነአባ የማነ ክርስቶስና ከሌሎች መናንያን ጋር ብህትውናቸን በዚች ቦታ ቀጠሉ፤ ስርዓተ - ምንኩስናንም ከአባ የማነ ክርስቶስ ተቀበሉ ፡፡
በ 1700 ዓመተ ምህረት በአፄ ዮሐንስ ቀዳማዊ ዘመን መንግስት መንበረ ጵጵስና ላይ የነበሩትና በ 16 ኛው የእስክንድርያ ፓትርያሪክ በብፅዕ አቡነ ዮሐንስ ተሹመው ጥቅምት 1 / 1664 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፻ ኛው ጳጳስ አቡነ ሲኖዳ ሲሆኑ መንበረ ጵጵስ ናቸው ጎንደር ነበር ፡፡
ድል ባጃንም ወደ ጎንደር ሂደው ይችን ቦታ ታላቅነቷን ነግረው የክብር የአንድነት ገዳም እንድትሆን ጠየቁ ፤ጥያቄያቸውም በንጉሰ ነገስቱና በጳጳሱ ተቀባይነት አገኘ ፡፡ ተሳክቶላቸውም በደስታ ተመለሱ።
በ 1700 ዓ.ም የክብር የአንድነት ገዳም በመሆን ገዳማዊ ህይወት በግንደወይን በአባ ድል በጃንና በአባ የማነ ክርስቶስ ተጀመረ ፡፡ ሁለቱ ቅዱሳን በቦታዋ ላይ የገዳም ህግና ስርዓተ ሰሩ መምህራንና ዲያቆናት በየ ማዕረጋቸው ሾሙ። በዚህ መሰረት የግንደወይን ማርያም ገዳም ተብላ ተሰይማ ዛሬ የአባቶቻችንን ስም በወረብ በቅዱስ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ልጆች ተዘክሯቸው ለዘላለም ይኖራል።
ጎንቻ ኮሙኒኬሽን መጋቢት 3/2017 ዓም

No comments:
Post a Comment