በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ፡
መተርጉማኑ መዝሙር ሁለትን በተረጎሙበት አምድ ላይ
“ላዕለ እግዚአብሔር ወላዕለ መሢሁ” የሚለውን ገጸ ንባብ
አንድ ጊዜ “በእግዚአብሔርና በመሢሁ ላይ” ብለው ሲያልፉት ሌላ ጊዜ ደግሞ “በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ ላይ” እያሉ ዋናዋን ቃል ላለመንካት ዳር ዳር በማለት ሲተረጉሙት በብራ የተጻፈው ትርጓሜ ላይ ግን “በእግዚአብሔር አብም መንፈስ ቅዱስን በቀባው ልጁም” በማለት ተተርጉሞ ይገኛል። ይህ ትርጓሜም የእነ ቅዱስ ቄርሎስን፣ የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ትርጓሜ የተከተለ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ማለት እንግዲህ ከስሙ ትርጓሜ ስንነሳ
ክርስቶስ - በጽርዕ፤
መሲሕ - በአረብ፤
ቅቡዕ - በግእዝ፤
የተቀባ - በአማረኛ ተብሎ ተተርጉሞ በመጽሐፍት እናገኘዋለንና። ዮሐ ፩፥፵፩ ትርጓሜ፤ መጽ ምስጢር 20፥40።
ሌላው ደግሞ መዝሙር 44 ላይ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ስለ ክርስቶስ የተናገረበት ትንቢት ነው።
“መዝሙረ ዳዊት ንባቡና ትርጓሜው” በማለት በ1950 ዓ/ም የታተመውና ከዚያ ጀምሮ ወልድ ቅብዕ ባዮች(ካሮች) “ከጥንት ከኢትዮጵያ ሊቃውንት ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ” በማለት በማር የተለወሠ መርዛቸውን ለትውልድ ሲግቱ እንደሚከተለው እናየዋለን።
"ተከዕወ ሞገስ እምከናፍሪከ ፤ በእንተዝ ባረከከ እግዚአብሔር ለዓለም -- ካንደበትህ ባለሟልነት ሞልቶ ፈሰሰ፤ ስለዚህ ነገር እግዚአብሔርነትህ ለዘላለሙ በተዋሕዶ አከበረህ” ብለው የሌለ ትርጉም፤ እንግዳ ትምህርት በማስገባት ተርጉመውታል።
ከብራናው ላይ ግን ““ተከዕወ ሞገስ እምከናፍሪከ --
ስርየተ ኃጢያት፤ ትምህርት ከአፍህ እንደ ውኃ ፈሰሰ።
……………………….
“አፍቀርከ ጽድቀ ወአመፃ ጸላዕከ --- ሐሰት ጠልተህ እውነት ወደህ ሰው ሆንክ፤
በእንተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ--- ቀድሞ የባሕርይ ልጅ የባሕርይ ንጉሥ ነበርክ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ ንጉሥ ትሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ቀባህ።
ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ -- ቅብዓቱም እንዳንተ ካሉ ከምእመናን እጅጉን የሚሻል የትፍሥሕት ቅብዓት ነው።” ተብሎ በትክክለኛ ተተርጉሟል።
ወልድ ቅብዕ ባዮች ደግሞ “አፍቀርከ ጽድቀ ወአመፃ ጸላዕከ ---
እውነትን ወደድህ ሀሰትን ጠላህ……….
በእንተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ ፟---
ሰው መሆንን ስለወደድህ አለመሆንን ስለጠላህ ፈጣሪህ እግዚአብሔር አዋሐደህ
ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ--- እንዳንተ ያሉ ነቢያት፣ ካህናት ከተቀቡት ልዩ የሚሆን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት ልዩ ተዋሕዶን አዋሐደህ” በማለት አጣመው ተርጉመውታል።
ቅዱስ ዳዊት እኮ "ዘይኄይስ እምእለ ከማከ--እንዳንተ ካሉት ይልቅ" ብሎ ለንጽጽር ያቀረባቸው ካህናት፣ ነገሥታት፣ነቢያት ናቸው። ቢሾሙ፣ ቢነግሡ፣ ትንቢት ቢናገሩ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ነው እንጅ በተዋሕዶ አይደለምና። የክብር መገኛው ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ እንጅ ተዋሕዶ አይደለም። ተዋሕዶ ሁለት መባልን በማስተው አንድነትን ያጸናል እንጅ ክብር አያስገኝምና።
ሥለዚህ "ቅብዓ ትፍሥሕት -- የደሥታ ቅብዓት" ተብሎ የተነገረው መንፈስ ቅዱስ እንጅ እንደ ዘመኑ መምህራን እንደሚሉት "ልዩ ተዋሕዶ" ተብሎ በፍጹም ሊተረጎም አይገባም።
ለዚህም ምስክር ዮሐንስ አፈ ወርቅ ድር 3 "እስመ ለእግዚእ ክርስቶስ አኮ በመስፈርት ዘተውህቦ መንፈስ -- ለክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በልክ በመጠን የተሰጠው አይደለምና"፤ ቅዱስ ቄርሎስም "ቅብዓ ነከራ -- የሚደንቅ፣ ልዩ ቅብዓት" በማለት ይገልፀዋል። ዕብ 1፥9 አንድምታ
የብሉይ ኪዳን ነቢያት፣ ካህናት፣ ነገሥታት ከማን ጋር ሲዋሐዱ ኖረው ነው ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ የእርሱን ከፍጡራን ለመለየት "ልዩ" ተዋሕዶ ብለው ለመናገር የደፈሩት?
አንባቢው ያስተውል "የክርስቶስን መሢሕነት" ክደው ማንን እንደሚያመልኩ ባለቤቱ ይወቀው!
የብራናው ትርጓሜ ዳዊት የተገኘው ከፈረንሳይ ዲጅታል ቤተ መጽሐፍት ነው።
ይህ ጽሑፍ ለታሪክ ይቀመጥ እንጅ በተዋሕዶ ከበረ፣ ወልድ ቅብዕ ብዮችስ ላይመለሱ በክህደት አረንቋ ከወደቁ ቆይተዋል።
ከላይ ያለው መዝሙር 2 ነው።
No comments:
Post a Comment