በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
=====+=====+====
ጾመ ነቢያት መቼ ፤ ለምን ( ክፍል አንድ)
====+===+====
ኦርቶዶክሳዊው ጾመ ነቢያት በዐራቱም ዘመናት (በማቴዎስ ፣ በማርቆስ ፣ በሉቃስ ፣ በዮሐንስ) ኅዳር 19 ቀን ይገባል ታኅሣሥ 29 ይፈታል።
------------------------------------------------------------
ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር አዳምን በአርያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በፈጠረው በ40 ቀኑ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ገነት አስገባው ፡፡ አዳም ግን በደለ ፤ ከገነትም ተባረረ ፤ በምድረ በዳዋ በደብረ ቅዱስም ተቀመጠ ፤ በጥንተ ጠላቱ ሠይጣንም ሥቃይና መከራን ተቀበለ ፡፡
በዚህም አንጻር በ40 ቀኑ ያጣትን ገነትን ያወርሰው ዘንድ ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይወርዳል ይወለዳል ፤ አዳምንም ከግዞት ከባርነት ነጻ ያወጣዋል ብለው ነቢያት የጾሙት ጾም ነው ፡፡ ጾሙ 40 መዓልት 40 ሌሊት ነው ፡፡ “ጾመ ሙሴ ዐርብዓ መዓልተ ወዐርብዓ ሌሊተ” እንዳለች ኦሪት ፡፡ ከ40 ቀን በላይ ጾመ ተብሎ የተጻፈለት አንድም ነቢይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም ፡፡ 40 ቀን የሚሆነው ጾሙን ኅዳር 19 ስንጀምር ነው ፡፡
ነገር ግን “62ኛው የግብጽ ጳጳስ አብርሃም ሶርያዊ ሦስት ቀን በመጾም ተራራ አንቀሳቅሶ ከመናፍቃን ሕዝቡን ያዳነባት ጾም ናትና ከ40ው ጾም ጋር መጨመር አለባት” እያሉ የሚከራከሩ ሰዎች አሉ ፡፡ እየጾምነው ያለነው ጾም ደግሞ ጾመ ነቢያት እንጅ ጾመ አብርሃም ሶርያዊ አይደለም ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ አንድ ቀን አብርሃም ሦርያዊ፣ አንድቀን ጋድ፣ አንድ ቀን ጾመ ፊልጶስ፣ አንድ ቀን በዓለ መበስር በዓለ አብሳሪ የሚሉ ነገሮችን እየቀላቀሉ ማምጣት ጀምረዋል። የትኞቹ ቀናት ናቸው ቢባሉ መልስ የላቸውም። አብርሃም ሶርያዊና ፊልጶስ የጾሙትን ጾም የነቢያት ጾም ነው ብሎ ልቡናቸው እንደፈቀደ ማወጃቸው ግን ተገቢነት የለውም ፡፡ በጾም ምክንያት ክርክር ቢደረግ ለጾም አድሉ ብሏልና መጽሐፍ ብንጾም ባልከፋ ነበር ፡፡ ነገር ግን በቀኖና ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ የተጨመረውን ጭማሪ ቀን ያልጾሙትን መናፍቃን እያሉ መሳደብ ተገቢ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም ሦስቷ ቀን በሲኖዶስ የተደነገገች አይደለችም ፡፡
እነዚህ ሰዎች ለዚህ እንደማስተባበያ የሚያቀርቡት “ጌታ የጾመው ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ሲሆን የእሱ ጾም ከመጀመሩ በፊት ጾመ ሕርቃልን ከእሱ ጾም በኋላ ደግሞ ሕማማትን እንጾማለን፤ታዲያ እሱ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾሟልና ዐርባውን ብቻ ለምን አንጾምም ስለምን ከዐርባ በላይ ቀናትን እንጾማለን?” የሚል ሀሳብን ነው ፡፡ እንደ አስተሳሰባቸው “ልክ ከዓቢይ ጾም ጋር ጾመ ሕርቃልንና ሕማማትን ከጌታ ዓርባ ቀንና ሌሊት ጾም ጋር ደርበን እንደምንጾም ሁሉ ይህችን ሦሥቷን ቀንም እንደዚያ እንጾማታለን” ማለታቸው ነው፡፡
ይህ ከንቱ ሀሳብ ፈጠራቸውን እውነት ለማስመሰል ያመጡት ነው ፡፡ ምክንያቱም ስለ ሰሙነ ሕማማት “ወበሰሙነ ሕማማት ኢትብልዑ ወኢምንትኒ ዘእንበለ ኅብስት ወፄው ወማይ (በሕማማት ሳምንት በጨው ከተሠራ ቂጣና ከውሀ በቀር ምንም አትብሉ አትጠጡ) ፤ ተዐቀቡ በዝንቱ መዋዕለ አጽዋም እምበሊዐ ሥጋ ወእምሰትየ ወይን እስመ መዋዕለ ላህ ወኀዘን እማንቱ ፤ ወፈድፋሰ በእሉ ሰዱስ ዕለታት(በዚህ የጾም ወራት ሥጋ ከመብላት ጠጅ ከመጠጣት ተጠበቁ ፣ የለቅሶና የኀዘን ቀኖች ናቸውና ፤ ይልቁንም እነዚህን ስድስቱን ቀናት” ዲድስቅልያ አንቀጽ 30 ቊ 10-11 ተብሎ ተነግሯል ፡፡
“ወበእንተዝ ንኤዝዘክሙ ትጹሙ ከመ ገበርነ ንሕነ (ስለዚህ እኛ እንደሠራነው ትጾሙ ዘንድ እናዝዛችኋለን” አንቀጽ 30 ቊ 15 እንዳሉን በታዘዝነው መሠረት የምንጾማቸው እንጅ እንዲሁ በዘፈቀደ መጥተው ከዐርባው የጌታ የጾም ቀናት ጋር የምንጾማቸው አይደሉም፡፡ ፍትሐ ነገሥትም “ወእምኔሆሙ ዘይከውን በአምሳለ ዐቢይ ጾም በተጠናቅቆ (ከእነዚህም እንደ ዐቢይ ጾም በጥንቃቄ የሚሆን አለ)፤ወይእቲ ሰሙነ ሕርቃል ዘትከውን እምቅድመ ጾመ ዐቢይ(ይህችውም ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትን የሕርቃል ጾምናት) አንቀጽ 15 ተብሎ ተገልጦ ስለተቀመጠልን እንጅ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚሆኑ አይደሉም ፡፡
በመሆኑም “ናሁ ጸሐፍነ ለክሙ ዘንተ ኵሎ ኦ ፍቁራን አኃው ትለብው ጥበበ ወአእምሮ ወኢትትወከፉ ነገረ ፅሩዐ ዘገብሩ ዕልዋን በስመ ዚአነ(የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ጥበብንና ዕውቀትን ታስተውሉ ዘንድ ይህንን ጻፍንላችሁ፤ወንጀለኞች በእኛ ስም የሚያደርጉትን ተርታ ነገርም አትቀበሉ)” ዲድስቅልያ አንቀጽ 33 ቊ 99 ብለው ሐዋርያት በጻፉልን መሠረት ላይ ታንጸናልና በተራና በተርታ ነገር አንታለልም ፣ ከሐዋርያት አባቶቻችን ድንጋጌ ፈቀቅ አንልም ፡፡
መቼም እኛ እንመራ የነበረው በውጭ ጳጳሳት ስለነበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ላይ እንደነ ቄርሎስ ዐራተኛ እና ሣልሳዊ ሰላማ ያሉ ብዙ መናፍቃን ጳጰሳትንና በዘመነ ሱስንዮስ እንደተደረገው ሁለተኛ ጥምቀት ዓይነት ብዙ የሥርዓት ለውጦች ደርሰውባታል ፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በአሠርቱ ወአሐዱ ምዕተ ዓመት ሙስሊሙ ጳጳስ ተብሎ መጥቶ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል ፡፡ እናም በሐዋርያት ሲኖዶስ ያልተደነገገውን ሥርዓት በግዳጅ 40ውን ጾም 43 ወይንም 44ት አድርጋችሁ ካልጾማችሁ መናፍቅ ናችሁ ማለት “እንዘቦ በክሕደት ያወግዙ ካልአ” ያሰኛል ፡፡
ምክንያቱም ሐዋርያት ነቢያት ባለቤቱ ክርስቶስ የጾሙት 40 መዓለት 40 ሌሊት ነውና ፡፡ ጾሙ ዓመቱን ሙሉ (ከበዓለ ሐምሳ ፣ ከሰንበት ፣ ከልደት ፣ ከጥምቀት ዕለታት ውጭ) ቢጾሙ በረከት ያስገኛል ፤ በአዋጅ ከታወጁት ከ7ቱ አጽዋማት ውስጥ የማይመደቡ በግል በፈቃድ የሚጾሙ አጽዋማትን አለመጾም ግን ክብር በረከት አያሳጣም ፡፡ ስለዚህ የምትጾሙ ወገኖቻችን ዝም ብላችሁ ጹሙ ፤ በሐዋርያት ሲኖዶስ ያልተወሰነ ያልተደነገገ ጾምን ያልጾመ ሰው መናፍቅ ነው ከሐዲ ነው እያላችሁ ግን ጊዜአችንንም ጉልበታችንንም ሁለመናችንንም አትበዝብዙብን፡፡ ወይ ተማሩ አልያም ጸጥ ብላችሁ የራሳችሁን ኑሩ ፡፡
አንባቢው አስተውል እኒህ ጠማሞች ይህችን ግዳጅ የምትለዋን ቃል ለመዘነጣጠል እንዳይጠቀሟት ፍራ ፡፡ ልቡናቸው የዞረ ስለሆነ “እነዚህ ቅብዓቶች ጾምን ግዳጅ ይላሉ” ማለታቸው ስለማይቀር ለምን ግዳጅ እንዳልን ማብራሪያ እንስጥባት ፡፡ በሐዋርያት ሲኖዶስ ያልተወሰነውን ቀኖና በሐዋርያት ሲኖዶስ የተወሰነ አስመስለው ዘንቀው በራሳቸው ጨምረው የነቢያት ጾም ያይደለችውን ጾም ራሳቸው ፈጥረው ቀኖናውን ካደሱ በኋላ እናንተ እኮ ሃይማኖት የላችሁም በማለት ምእመናንን ድጋሚ እያጠመቁ ከቀኖና እድሳት ወደ ሃይማኖት እድሳት የሚጓዙባት የክሕደት ሠረገላቸው ስለሆነች ግዳጅ አልናት እንጅ ጾምን ግዳጅ ማለታችን እንዳይደለ አስተውል ፡፡
በዚያውም ላይ ትጾማለች የሚሉትም ሰዎች ቢሆኑ መቼ ይጀመር በሚለው አይስማሙም ፡፡
እኩሉ በ15 መጀመር አለበት ብሎ በፍትሐ ነገሥቱ ላይ መንፈቁ ለኅዳር የሚል ሥርዋጽን አስገብቶ ሲናገር እኩሉ በ16 ይሏል ፣
እኩሌቶቹ ደግሞ በዘመነ ዮሐንስ በ14 ይጀምራል የሚሉም አሉ ፡፡ ይህ በዘመነ ዮሐንስ ነውና ልደቱን ከ29 ወደ 28 ጎትተው ለውጠው ከዓለም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት በተለየ መልኩ “ወልድ ቅብዕ፤ ቃል ቀባዒና ቅብዕ ፤ ትስብእት በቃል ተቀባዒ” ብለው እንደለዩት ሁሉ ታኅሣሥ 29 የተወለደ ጌታን ታኅሣሥ 28 ተወለደ ብለው በዓለ ልደትን ብቻ ወደ ኋላ አንድ ቀን መልሰው የሚያከብሩ ሰዎች በ14 ካልጀመርን ቀን ይጎድልብናል ብለው የፈጠሩት ልብወለድ አነጋገራቸው ነው ፡፡ በየሠፈራችሁ ነገ ጀምራችሁ መታዘብ ትችላላችሁ ፡፡ ይሁን እንጂ በ14ትም ይጀምሩት በ15ትም ይጀምሩት በ16ትም ይጀምሩት በዘመነ ዮሐንስ በ28 ስለሚገድፉ (ስለሚፈስኩ)የጾሙት ጾም ሁሉ ይፈርሳል እላለሁ ፡፡ ምክንያቱም ጾመው ጾመው አንድ ቀን ሲቀራቸው ያፈርሳሉና ነው ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘመነ ዮሐንስ በ14 ነው የምንጀምር የሚሉ ሰዎች እኔ ግን ምናልባት እርሷም ግእዘ ሕፃናትን ታፍልሳለች ተብሎ ይሆንን! ብየ እጠይቃለሁ ፤
አንዳንዶች ደግሞ በሥንክሣር መንፈቁ ለኅዳር የሚል ሥርዋጽ አስገብተው በ16 መጀመር አለበት ይላሉ ፡፡
እኔ እንደ አንድ ኦርቶዶክሰዊ ምእመን ሰዎቹ እኛን መናፍቃን ናችሁ ከማለታቸው በፊት እስኪ ራሳቸው በመጀመሪያ ከእንዲህ ዓይነት ልዩነት ነጻ ይሁኑ እላለሁ ፡፡
በተጨማሪም በ28ም በ29ኝም ጌታን የወለደችበት ነው ከሚለው ዓይን ያወጣ ውሸትም ራሳችሁን ነጻ አድርጉ በሉልኝ።
ከዚህ ሁሉ ግሳንግስና መለያየት ነጻ ሁነን በየዓመቱ ለእመኮነና ኢየዓርግ ኢይወርድ ያልተሠራላትን ጾመ ነቢያትንና አንዲት ኦርቶዶክሳዊት ልደተ ክርስቶስን ሐዋርያት በሠሯት ሥርዓት እንድናከብር ያደረጉ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን በረከታቸው አይለየን ፡፡
ማሳሰቢያ፡- ይችን ጾም አኀት አብያተ ክርስቲያናት መቼ እንደሚጀምሩ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ስለሆነ በውጩ ዓለም የምትገኙ እህት ወንድሞቻችን መረጃ ብትሰጡን ወይም ደግሞ መጻሕፍት ካሉ ብትጠቁሙን እላለሁ ፡፡
ስለ ልደተ ክርስቶስ በቅርቡ እጽፋለሁ
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኃኒትነ
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ
አሜን!
በዲ/ን ብርሃኑ ሻምበል
No comments:
Post a Comment